ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) ‹‹ኢትዮጵያዊያን ታሪክ መስራት ይችላሉ››

Views: 43

ኢትዮጵያዊያን በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በመያዝ ታሪክ መስራት ይችላሉ ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቷ በሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡት ፓርኮች በትብብር ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ማሳያ ናቸው ብለዋል።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛና የተለያዩ ሁነቶች የሚከወኑበት አስደናቂ ፓርኮችን ማግኘቷ ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ሸገር ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በከተማዋ የተገነቡ ፓርኮች የከተማዋን እንዲሁም የአገሪቱን ገጽታ በመለወጥ ትልቅ አስተዋጾ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው” ተስማምተንና ተግባብተን ያለንን አቅም አሰባስበን በጋራ ፍላጎታችን ላይ ስንዘምት ታሪክ መስራት እንደምንችል ህያው ምስክር ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ያላቸው ሃብትና ውበት አንድነትንና የተሻለ ህይወትን አጣምሮ ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህንን ለማድረግ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ አቋም በጽናት መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ።

አሁን ከተገነቡት ከፓርኮች ልምድ በመውሰድ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ክፍት ቦታዎች መጠነኛ ፓርኮችን መስራት እንደሚቻልም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ከተማዋን ለማስዋብ ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከተማዋን ከማስዋብ ጎን ለጎን ዋና ትኩረት ለሆነው የልማትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረና መተዳደሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣
ሸገር ፓርክ ብዙ የህዝብ መዝናኛ የሏትም ተብላ ለምትተቸው አዲስ አበባ በሌላ ከፍታ የሚያስቀምጣት መሆኑን ገልጸዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com