ፌጦ በኢትዮጵያ (የአዲስ ዓመት ብሥራት)

Views: 190

“መስከረም ፩ በማለዳ”  …  

“ወዳጄ፣ ለማንኛውም ፌጦ መድኃኒት ነው!” ሲባል አልሰማህም…

መቅድም:-

ፌጦ፡- በሳይንሳዊ መጠሪያ  (Lepidium sativum)   በኦሮሚኛ Feexoo (Oromiffan)፣  በእንግሊዘኛ Garden cress (English)፤   በፈረንሳይኛ cresson alénois (French)  እና በጀርመንኛ  Gaetnkresse (German) ተብላ ትጠራለች፡፡

በቀደመው ልማድ በገጠረም በከተማም በብዙዎች ደገኞች አካባቢ መስከረም አንድ ማለዳ ከምንም ምግብ በፊት የሚቀመሰው ወይም የሚበላው ፌጦ ነው፡፡ አመቱን ሙሉ በሽታን ለማራቀ ሲባል መስከረም አንድ ማለዳ ፌጦ ለምግብነት ይውላል፡፡

አቀራረቡም፡- ፌጦው ይደቆሳል፣ በሎሚ ጭማቂ ውሃ እና በውሃ ይለወሳል፣ ጨው ጣል ይደረጋል፣ በእንጀራ ይፈተፈታል፡፡ ፍትፍቱ፣ በአንድ ጉርሻ ያህል ተመጥኖ በትንንሹ ቁጭ፣ ቁጭ ይደረጋል፡፡ የቤተሰቡ አባላት እየቀረቡ ተራ በተራ ወስደው ይበሉታል ወይም ዋጥ ያደርጉታል፡፡ ጥቂቶች በደስታ ይሻሙታል፣ ምን አልባት በርካቶች ደግሞ “እቅ” እያሉ ፊታቸውን አጨፍግገው ይውጡታል፡፡ የተወሰኑት ጥሟቸው ድጋሚ ሊጎርሱ ይችላሉ፤ የፈሩቱ ደግሞ የግዴታ ያህል አንዷን ጉርሻ እንደምንም ዓይናቸውን ጨፍነው ዋጥ ያደርጋሉ፡፡

በሌላም በኩል፣ በኢትዮጵያ የባሕል መድኃኒት ውስጥ ትልቁ ባለዝና ፌጦ ነው፡፡ ለዚህ ነው “ወዳጄ ለማንኛውም ፌጦ መድኃኒት ነው” የሚል አባባል ጣል ሲደረግ እንደዋዛ የምንሰማው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የፌጦ መድኃኒትነት ከተባለለትም በላይ ነው፡፡ ፌጦ መቸም ቢሆን በግልጽ የሚነገር የባሕል መድኃኒት እንጂ፣ የሚደበቅ አልነበረም፡፡  ስለዚህ፣ የፌጦን መድኃኒትነት ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰው የተባለውን ያህል አልተጠቀመም፡፡

በመስከረም አንድ ማለዳ ፌጦ መቅመስ እና ለማንኛውም ፌጦ መድኃኒት ነው የሚባለው ብሂል፣ ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ መቸም ቢሆን፣ ለማንኛውም ሕመም፣ አመቱን ሙሉ፣ ለሰውም፣ ለቤት እንስሳትም፣ ፌጦን አትርሱ፤ በአግባብ ተጠቀሙ የሚል መልዕክት ያለው ይመስላል፡፡

ነገር ግን፣ እንደ ተረቱ  “ዕውቀት በደሃ ቤት ነበርሽ! …. ማን ጆሮ በሰሠጠሽ!” እንደተባለው ሆነና፣ ማን ፌጦን ከዋጋ ቆጠረ!? በብዙ መረጃ ላይ የፌጦ መገኛ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ነገር ግን በጣም የተገለገሉበት አገራት እነ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያ እና ጀርመን ናቸው ብሎ የሚነግረን፣ ቤን ኤሪክ ቫን ዊኪ ነው፡፡ ማጣቀሻ አንድ

የሆነው ሆኖ፣ የሚከተለውን አስተውሉ፡-

የፌጦ አዝመራ፡-

ፌጦ መደቡ ከቅመማ ቅመም ወገን ሲሆን፣ በአገራችን ማሳ ሙሉ ሳይሆን፣ ከሌላ እህል ለምሳሌ ከተልባ ጋር፣ ከሌሎች ሰብሎች ዳርቻ እና በጓሮ ነው የሚዘራው፡፡ በተዘራ እስከ 3 ወራት ጊዜ ውስጥ ይደርሳል፡፡ በዋናነት ቀይ እና ጥቁር ፌጦ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በብዛት የሚመረተው ደግሞ ቀዩ ነው፡፡ አነሰም፣ በዛም በአገሪቱ ደጋ እና ወይና ደጋ የሰብል አዝመራ በሚታረስበት አካባቢ ይመረታል፡፡ እንደሌሎቹ ትኩረት ያልተሰጣቸው ሰብሎች፣ ፌጦንም “አባከና” ያለው የለም፡፡ ስለዚህ፣ በምርምር የደገፈው የለም፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለዘመናት ሁሉንም ሰብሎች፣ አንብረው፣ ጠብቀው፣ አልምተው እንዳቆዩት ሁሉ ፌጦንም ለዚህ ዘመን አደረሱት፡፡

የፌጦ ተክል ገና እያፈራ ሳለ

የፌጦ ገበያ፡-

ፌጦን ያመረቱት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ከተማ ወስደው ይሸጡታል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በአገሪቱ ገበያ ላይ በአብዛኛው የሚሸጡት በአነስተኛ መጠን ቅመማ ቅመም ሻጭ ሴቶች ናቸው፡፡ የሚገኘውም ከእነርሱ ዘንድ፣ ከሌሎች ቅመማት ጋር ተሰልፎ ተዘርግቶ፣ ወይም ተቋጥሮ አንዳች ዕቃ ውስጥ ነው፡፡ ሲጠየቁ ከተቋጠረበት በርብረው ያወጡታል፡፡ በቅርቡ ዘመናት በየቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ በትልልቅ ዕቃ (በጆክ፣ በብርጭቆ) እየተሰፈረ መሸጥ ተጀምሯል፡፡ ይልቁንም ዘንድሮ የሁሉም ቅመማት ፍለጋ ከፍ በማለቱ፣ እንዲሁ ፌጦም በገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊ እና ተወዳጅ ሆኗል፡፡

1ኛ/ የፌጦ መድኃኒትነት ለምንድነው?

ፌጦ ቅጠሉ ራሱ ፀር ተውሳክ ነው፣ ፍሬው ለሆድ መድኃኒት ነው፤ ለውጪ አካል ይቀባል፣ ብቻውን ይወሰዳል ወይም ከሌሎች ጋር ይቀመማል፡፡ ፌጦ ብዙ ሙያ አለው፡፡ ቀጥሎ በዝርዝር እንመልከት፡፡

ከህክምና በቤታችን መጽሐፍ ላይ እንደተወሰደው፤ ማጣቀሻ ሁለት

ሀ) የአቶ ገላሁን ሥራ ከሆነው ዕፀ ደብዳቤ (1975 ዓ.ም ከተዘጋጀው) ላይ ስለ ፌጦ እንደዚህ ይላል፤

 • ለላሽኝ የበርበሬ ፍሬ፣ የድንጋይ ልብስ፣ አረግ እሬሳ ቅጠል፣ ፌጦ በአንድ ላይ ደቁሰህ በቅቤ ለውሰህ መቀባት ነው፡፡
 • መድማትን ለማስቆም፣ የአጋም ሥር፣ የችፍርግ ሥር፣ የጐመሮ ሥር፣ የብሳና ሥር፣ ፌጦ፤ በአንድነት አድርጐ መቀባት ነው፡፡

ለ) የሕዝብ ዕውቀት

 • ለከንፈር ምች፤  የፌጦ ፍሬ ወቅጦ ወይም ደቁሶ በውሃ መለውስ እና ቀብቶ አድሮ ጠዋት፣ ፀሐይ ሳይነካው በፊት በልብስ ሳሙና መታጠብ ነው፡፡
 • ለአጣዳፊ አሜባ ወይም ጃርድያ አንድ የሻይ ማንኪያ የተወቀጠ ፌጦ፣ በአንድ የሾርባ ማንኪያ ማር ለውሶ ጠዋት በባዶ ሆድ እና ማታ ከመኝታ በፊት ለ4 ቀናት መዋጥ ነው፡፡
 • አሜባ ወይም ጃርድያ እየተደበቀ፣ የሚያሰቃይ ከሆነ፣ ጥቁር ፌጦ ጥሬውን አንድ ሾርባ ማንኪያ ያህል፣ በአንድ ብርጭቆ ውሃ ላይ በትኖ፣ ከትንሽ ጨው ጋር ዘፍዝፎ ማሳደር ነው፡፡ ጠዋት አንድ ሎሚ ጭማቂ ውሃ ጨምሮ፣ በአንድ ላይ እንደ አብሽ መምታት እና ማዘጋጀት፡፡ ከዚያም አሜባ ወይም ጃርድያ እራሱን ከሚደብቅበት የሰውነት ክፍል ውስጥ እንዲወጣ ለማድረግ ማታለያ ዘዴ ማድረግ ነው፡፡ ዘወትር እሱን የሚቀሰቅስ ምግብ ምን እንደሆነ መለየት፣ ለምሳሌ ጥሬ ቲማቲም ቢሆን፣ ወተት ቢሆን ወዘተ፡፡ ያን ቀስቃሽ ምግብ በትንሹ ተመግቦ መታገስ፡፡ አሜባው ሆድ ውስጥ ትርምሱን ሲጀምር፣ ወድያው ያን የተመታ ፌጦ መጠጣት፡፡ እስከ ምሳ ሰዓት ምንም ምግብ እና መጠጥ ክልክል ነው፡፡ በምሳ ሰዓት ለስላሳ ምግብ መብላት፡፡ ለሶስት ቀናት በተከታታይ ማለዳ እንዲሁ ቢደረግ በሽታው ድራሹ ይጠፋል፡፡
 • ለችፌ ቁስል፣ የኮሶ ፍሬ፣ ፌጦ፣ ጨው እና ከጭስ ቤት ላይ ጥቀርሻ ሰብስቦ ደቈሶ በቅቤ ለውሶ ቁስሉን ጠዋት ማታ ማጠብ እና መቀባት ያድናል፡፡
 • ለሄርበዝ ዞስተር ቁስል፣(አልማዝ ባለጭራ) እና ንብ ስትነድፍ፣  ነጭ ሽንኩርት እና ፌጦ፣ ፈጭቶ በባዝሊን ለውሶ ቁስሉን መቀባት ከሚለበልበው ሕመም ያስታግሳል፡፡
 • የቫይቫክስ ወባ ሕመምን ለመከላከል፣ የተወቀጠ ፌጦ፣ የሎሚ ውሃ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ እና ጨው በአንድነት በማዋሃድ በእንጀራ ዘወትር መመገብ በሽታው እንዳይዝ ለመከላከል ይረዳል፡፡ በሽታውም ጀምሮ ሕክምና እየወሰዱ ቢሆን፣ ጎን ለጎን ይህንን ድቁስ መጠቀም ይቻላሉ፡፡
 • ለዶሮ ቅዘን ማከሚያ፣ አንድ የሻይ ማንኪያ የፌጦ ዱቄት ለ 5 ዶሮዎች መጥኖ ከሚመገቡት ጋር አዋህዶ በቀን አንድ ጊዜ፤ በየሁለት ቀን መስጠት ነው፡፡

ሐ) ከመጽሐፈ መድኃኒት፣

 • ለሐሞትና የልብ ቃር መድኃኒት  ፌጦ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ እኩል እኩል  አድርጎ ፈጭቶ በተነጠረ ማር ለውሶ ጧት ጧት በባዶ ሆድ በትንሽ ማንካ ፩ ይበሏል፡፡
 • ለሆድ በሽታ፣ የፌጦ፣ የአሜራ ፍሬ፣ የሮማን ቅርፊት፣የተምር፣ የቀረጥ ልጥ፣ ጦስኝ፣ ከ ፯ ጥዋ ውሃ ፩ ሲቀር ብትጠጣ ትፈወሳለህ፡፡
 • ለትኩሳት ወይም ለምች፣ ሬት፣ ዝንጅብል፣ ፌጦ ደረቁን ሁሉንም አስተካክለህ ነጭ ሽንኩርት ደቈሰህ ብትበላ ትድናለህ፡፡

2ኛ/ ፌጦን ለሳል፣ ለጉንፋን እና ለመሳሰሉት እንዴት እንጠቀም!?

ማንኛውም ዓይነት ሳል ወይም ጉንፋን በያዘ ጊዜ ሕመሙ ቶሎ እንዲድን ፌጦን መጠጣት ነው፡፡ መጀመሪያ ጥሬው ቀይ ፌጦ ይለቀማል፡፡ በቀላሉ የሚፈጭ ማሽን ካለ መፍጨት ነው፡፡ ወይም በወፍጮ ላይ ውሃ ጠብ እያደረጉ መለንቀጥ (መደቆስ) ነው፡፡ ለምሳሌ ከታች በምስሉ ላይ በግራ በኩል ያለው ሁለት ሻይ ማንኪያ ቀይ ፌጦ ዘር ነው፡፡ በወፍጮ ከተለነቀጠ በኋላ በቀኝ እንደሚታየው ይበረክታል፣ ይለደልዳል፡፡

ፌጦ በግራ ጥሬ፣ በቀኝ በወፈጮ የተለነቀጠ፣

ከዚያም ትንሽ ውሃ እና ጨው ማከል እና ለ1ዐ ደቂቃ ያህል ማንተክተክ ነው፡፡ ሲንተከተክ ማቃጠሉ ይጠፋል፣ ይጣፍጣል፣ አንድ ስኒ መጠጣት ይቻላል፡፡ ጣዕሙ ከጥሬው ፌጦ የተለየ ነው፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ቢጠጣ ይበቃል፡፡ ማር ማከል ቻላል፡፡

የፌጦ ልንቅጥ እንደ ሾርባ ከተፈላ በኋላ

ሌላውንም ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለመሳሰሉት ይረዳሉ የተባሉትን ሁሉ፣ እየተጠቀማችሁ፣ ደግሞ ፌጦን በዚህ ዘዴ አክሉበት፡፡ ግሩም ውጤት ታገኛላችሁ፡፡

3ኛ/ ጥቂት ፍሬ ፌጦ በማለዳ፣ የፌጦ ፍሬውን ለቅሞ በጠርሙስ ዕቃ አዘጋጅቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ ዘወትር ማለዳ ሲነሱ ወይም ከቤት ወጥተው ወደ ሥራ ሊሄዱ ሲሉ፣ በሁለት ጣት ቆንጠር አድርጎ (የሻይ ማንኪያ ሩብ ያህል)፣ በአንድ ብርጭቆ ውሃ ላይ በተን አድርጎ ወድያው መጠጣት ለብዙ ሕመም መመከቻ ይሆናል ተብሎ ፌጦ ብዙ ጊዜ ይወደሳል፡፡ በተለያየ ምክንያት ለሚከሰት የሆድ ቁርጠት፣ ጥሩ ያልሆነ የሰውነት ጠረን ያለ እንደሆን ለማስወገድም ይረዳል፡፡ ለወር ያህል የወሰዱ እንደሆን ቦርጭን ቀንሶ ሸንቃጣ ለመሆንም ያግዛል፡፡

4ኛ/ ፌጦ ቅጠሉን ለምግብ፤ በብዙ አገራት እና በእኛም አገር አንዳንድ ቦታ ፌጦ ቅጠሉ ብቻውን ወይም ከሌሎች ቅጠላት ጋር እንደ ጎመን ተሠርቶ ይበላል፡፡ ከማፍራቱ በፊት ገና ለጋ ሳለ አናቱ ተቀንጥቦ ይሰበሰብና ይሠራል፡፡ አናቱ ስለተቀነጠበ የቀረው የፌጦ አካል ብዙ ዘንግ ያፈራል፣ የዘር ምርቱ ይጨምራል፡፡ በሌሎች አገራት ይህ ቅንጣቢ ቅጠል፣ በብዛት ይሸጣል፣ ብዙ ምግብ ይዘጋጅበታል፣ ለምሳሌም ግሩም ሰላጣ ይሠራበታል፡፡

5ኛ/ ፌጦ ፍሬ ጉንቁል፤ ፍሬው ለጥቂት ቀናት እንዲጎነቁል ተደርጎ ለምግብነት ይሆናል፡፡ በጥሬው ወይም በእንፋሎት በጥቂቱ በስሎ ሰላጣ ላይ ተጨማሪ ይደረጋል፡፡ ይህ ከፍተኛ የአይረን መጠን ስለሚኖረው ደም ማነስ ለታመሙት በጣም ይረደል፡፡

6ኛ/ ፌጦ ለጋ ቡቃያ፤ በዕቃ ላይ ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት እንዲያድግ አድርጎ፣ የፌጦን ቡቃያ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህ በሰላጣ ወይ በሾርባ ላይ ተደርጎ ይበላል፡፡ ይህም በብዙ ማዕድናት የበለፀገ ምግብ ማለት ነው፡፡

7ኛ/ ፌጦ ለጓሮ ተክሎች መድኃኒት፤ በጓሮ ውስጥ ከሌሎች ተክሎች ጋር ፌጦ ይዘራል፣ ቅጠሉ ያድጋል፡፡ ድንገት በሌሎች ተክሎች ላይ በሽታ ቢከሰት የፌጦ ተክሉ ይታጨድ እና ይወቀጣል፣ በውሃ ይጨመቃል፣ በበሽታ በተጎዳው ተክል ላይ ይረጫል፡፡ ግሩም የተፈጥሮ የተባይ እና የበሽታ መከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፕል ዛፎች ባሉበት ጊቢ፣ ፌጦን ለዚሁ ብሎ መዝራት ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳች ተውሳክ በአፕል ዛፎች ላይ ቢከሰት የፌጦው ጭማቂ ይረጫል፡፡

8ኛ/ ፌጦ ውሻ እና ድመት ጊቢ እንዳያበላሹ፣ (ድሙሻ) በሳር መሬት እና በጓሮ ተክሎች ላይ እንዳይሸኑ፣ እንዳይፀዳዱ ሁነኛ መከላከያ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የፌጦ ዱቄት በጥብጦ መርጨት ነው፡፡ ድመትና ውሻ (ድሙሻ) የጊቢ ጽዳት ማበላሽታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ በሽታ የሚያስተላልፉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ በዚሁ አምድ ላይ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/3925   ላይ አንብቡ፡፡

9ኛ/ ሌሎች ተጨማሪ የፌጦ ሙያዎች፣ በአንዳንድ አካባቢ፣ እህል ለመውቃት አውድማ ሲዘጋች፣ የፌጦ ዱቄት በውሃ ተበጥብጦ ዙሪያውን ይረጫል፡፡ ወና የከረመ ቤት ጡንጅት ይጫጫስበታል፣ ፌጦም ይረጭበታል፡፡ በሌላ አካባቢ ደግሞ ፈረስ ስትወልድ፣ ምች እንዳይመታት ተብሎ ፌጦ ትረጫለች፡፡

ማጠቃለያ፡-

ፌጦ፣ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው፡፡ ምግብና መድኃኒት ብቻ ሳይሆን ፀረ ተባይ ጭምር ነው፡፡ ፌጦ ለብዙ ከባድ ሕመሞች ፈውስ ነው፡፡ በብዙ የንጥረ ምግቦች በተለይም ማዕድናት የዳበረ ነው፡፡ ሆኖም፣ ለምግብነት ማጎንቆል፣ ቡቃያውን ማዘጋጀት ወይም ቅጠሉን መመገብ ያስፈልጋል፡፡ በሰፊው የእርሻ ማሳ ያላችሁ፣ እባካች ፌጦን አምርቱና ወደ ገበያ አስገቡት፡፡ ብዙም ታተርፋላችሁ፣ ለተመጋቢውም የጤና በረከት ነው፡፡ በጓሮ ትንሽ ቦታ ያለው ቤተሰብ ደግሞ ፌጦን ቢዘራ አሊያም የመትከያ ሥፍራ ካጣ በእቃ ላይም ቢሆን በቀላሉ ብትተክሉት ይበቅላል፡፡

እንግዲህ መስከረም አንድ ቀን ማለዳ ሳትረሱ እንደተባለው የፌጦ ፍትፍት ተመገቡ፡፡ በመላው አገሪቱ እና በሌላም አገራት ያላችሁ ፌጦ ምን፣ ምን ሙያ ይሠራበት እንደሆነ ያወቃችሁትን ለሌሎቻችን አሳውቁን፡፡

መልካም አዲስ አመት!!!

                                                                 

ማጣቀሻ፡-

ማጣቀሻ አንድ፣   Ben-Erik Van Wyk, CULINARY Herbs & Spices OF THE WORLD, BRIZA

PUBLICATIONS  CK  pretoria, South Africa.

ማጣቀሻ ሁለት፣ በቀለች ቶላ (6ኛ እትም 2ዐ12 ዓ.ም) ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ

ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት፣ አልፋ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com