ዜና

ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) ‹‹ኢትዮጵያ ካሳለፈችው ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ውጣ ውረዶች ታሪክ ልትማር ይገባል›› ፖለቲከኞች

Views: 149

ኢትዮጵያ ካሳለፈችው ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ውጣ ውረዶች ታሪክ ልትማር እንደሚገባ ፖለቲከኞች ተናገሩ።ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ በዘርፉ ከፍ ያለ ድርሻ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገር እና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ ግብ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ለፋና ገልጸዋል።

ሀገራዊ ጉዳዮችን በቅንነትና አርቆ አሳቢነት ለመመልከት ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጼጥሮሰ፤ በሃገሪቱ የራቀው ሃገራዊ መግባባት ካለፉ ታሪኮች እንዳንማር አድርጓል ይላሉ።
ፕሮፌሰር በየነ በሃገረ መንግስት ግንባታው ታሪክ የነበሩ እንከኖች እና መልካም ጅማሮዎች ላይ የሚደረሱ የጋራ ስምምነቶች ዜጎች ተስፋ ለሚያደርጓት ጠንካራ ሃገር ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ዜጎቿ እንደሚመኟት እንድትሆን ጠንካራ የትብብር ስራዎች ከሁሉም ይጠበቃል ይላሉ።

ለአንድ ጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሃገራዊ ጉዳዮችን በቅንነት እና አርቆ አሳቢነት መመልከት ይገባል የሚሉት ፖለቲከኞቹ፤ አለም አቀፍ ተመክሮዎችን ከሃገር ነባራዊሁኔታ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ ለማድረግ መስራት ይገባልም ብለዋል።

ለሚፈለገው የዴሞክራሲ እና ጠንካራ ሃገር ግንባታ የፖለቲካ ኃይሎች የሃገር እና የህዝብ ጥቅምን አስቀድመው መስራት እንዳለባቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሊቀመናብርት ተናግረዋል።

ለሚታዩ ሃገራዊ አለመረጋጋት ምክንያት እየሆኑ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ቀዳሚ የሆነን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አሰተያየት ተሰጥቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com