ዜና

አደይ አበባ- ለውበት እና ለጤና

Views: 1666

አደይ አበባ (Bidens borianiana)

አደይ አበባ፡- ለውበት እና ለጤና

የመስቀል ወፍ እና-

የአደይ አበባ፤

ቀጠሮ እንዳላቸው-

መስከረም ሲጠባ፤

ማን ያውቃል!? …

ሲሉ ባለቅኔውን አብዬ መንግስቱ የተቀኙት ያለ-ነገር አይመስለኝም፡፡ የሁለቱ ዓመታዊ ግንኙነት ድንቅ ቢላቸው ይመስለኛል፡፡

አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ መነሻው (መገኛው) ኢትዮጵያ ነው፡፡ በእኛ አገር ብዙ የተዘፈነለት/የተዘፈነበት፣ ብዙ የተዘመረበት አበባ፣  አደይ አበባ ነው፡፡

በተለይም በአዲስ አመት ዋዜማ እና መባቻ መንገዱ ሁሉ፣ ገበያው ሁሉ፣ የሚፈካው በአደይ አበባ ነው፡፡ መስከረም አንድ በአዲስ አመት የመጀመሪያው ቀን  “አበባ አየሽ ወይ? ..ለምለም!…” የተባለለት፣ በዕለቱም ከእንግጫ ጋር በየቤቱ የሚታደለው፣ በደመራ ወይም በችቦ አናት ላይ ለድምቀት የሚታሰረው፣ በእሬቻ በዓል ዕለት ከሰርዶ ሳር ጋር የሚታሠረው  አደይ አበባ ነው፡፡

የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲገባ ማን ያውቃል … እንዲል- ባለቅኔው፡፡

በሳይንሳዊ መጠሪያ ቢደንስ ቦሪያኒያና (Bidens borianiana) ይባላል፡፡ አደይ አበባ ቀደምት መገኛ አገሩ ኢትዮጵያ ቢሆንም፣ ቢደንስ ተብለው የሚጠሩት ግን ሌሎች እጅግ ብዙ ዝርያዎች በመላው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የሴጣን መርፌ (Bidens pilosa   Black jack)፤ አንዱ ነው፡፡ አደይ አበባ እና የሴጣን መርፌ በዝርያ አንድ ቢሆኑም በግልጋሎት ይለያያሉ፡፡ አደይ አበባ፣ ለአበባው ፍካት እና ውበት በእኛ አገር ባለዝና ሲሆን፤ የሴጣን መርፌ በብዙ የአፍሪካ አገራት፣ በኤሽያ እና በሐሩራማ የአሜሪካ ግዛት ምስጉን የቆዳ ላይ መድማትን ማቆሚያ፣ የወባ፣ የታይፎይድ ወዘተ የተፈጥሮ መድኃኒት ነው፡፡

እራሱ አደይ አበባ ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ በቆላ፣ በወይና፣ በደጋ፣ የሚበቅለው ብዙ ዓይነት ነው፡፡  ትንንሽ አንድ ስንዝር ቁመት ያላቸው፣ መካከለኛ እና ሁለት ሜትር ቁመት ያላቸው ትልልቅ አገዳ መሳይ ዘንግ ያላቸው ሁሉ አሉ፡፡

አስተውሉ አደይ አበባ ከሌሎች መሰል ቢጫ አበባ ካላቸው ጋር ልዩነት አለው፡፡ ዱር በቀል እና ክብካቤ የተነፈገው ስለሆነ እየተመናመነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም፣ ቢጫ የሚያብቡ እነ መጭ ሳይቀሩ እየተቀጠፉ ለውበት ግልጋሎት ላይ መዋል ጀምረዋል፡፡

በአዳማ ናዝሬት ከተማ እና አካባቢዋ በቅርብ አመታት እየተስፋፋ የመጣ አንድ ባለ ቢጫ አበባ አረም አለ፡፡ ይህ እየተቀጠፈ ልክ እንደ አደይ አበባ ከሳር፣ ከአሪቲ፣ ከአጁባን ጋር አድርገው አስረው ይሸጡታል፡፡

አደይ አበባ እንደ መድኃኒት

አደይ አበባ የፍካቱ እና የውበቱ ዜና የጎላ ቢሆንም ስለመድኃኒቱ ብዙ አልተባለም፡፡

አደይ አበባ

ለመድኃኒት ሲለቀም እንዲህ ነው፡፡

በከተሞች አደይ አበባ የማግኛችሁ ዘዴ አሁን በመንገድ ዳር ሲሸጥ ነው፡፡ ለውበትም ለመድኃኒትም ስትሉ ሸምቱ፡፡

በገጠር አካባቢ ግን ከመስከረም እስከ ህዳር በመስክ ላይ ቢጫ አበባ አብቦ ይገኛል፡፡ አበባው ከመድረቁ በፊት የፈካው አናቱ ጭምር እየተቀነጠሰ ይለቀምና ይደርቃል፡፡ ከዚም ይፈጫል፡፡

 • ደርቆ የተፈጨው አበባ ከባዝሊን ጋር ተለውሶ ማታ ማታ የቆዳ ቁስል ላይ ወይም የፀሐይ ቃጠሎ የጐዳውን የሰውነት ቆዳ ሲቀቡት እንደመድኃኒት ያገለግላል፡፡
 • ለማድያት በቅቤ ተለውሶ ማታ ተቀብቶ አድሮ ማለዳ መታጠብ ነው፡፡

ልብ በሉ፣ ሲቀቡት ከፀሐይ መከለል ያስፈልጋል፡፡

ተጨማሪ ነገር፡-

 • ሕፃናት አበባውን በእርጥብነቱ ወይም አድርቀው ለሥዕል መስሪያ ሊገለገሉበት ይችላሉ፡፡
 • አደይ አበባ ለንቦች ሁነኛ መኖ ነው፡፡ ንብ አናቢዎች ነገሬ ብለው ቢዘሩት በብዙ ያተርፉበታል፡፡

ማጠቃለያ፡-

አደይ አበባው በወቅቱ ተለቅሞ ደርቆ፣ ደቆ ታሽጎ በንፁህ ዕቃ የተቀመጠ እንደሆን ድንቅ የቤት ውስጥ የተፈጥሮ መድኃኒት ይሆናል፡፡ ልማቱን ያቀደ ቢኖር ዘሩን ለመሰብሰብ ደግሞ አበባው ሲደርቅ ያፈራውን አናቱን በመልቀም ነው፡፡ ከዚያም ዘሩ አንድ ወር ከቆየ በኋላ ለመዝራት በሚፈለግበት ጊዜ፣ ቦታ አዘጋጅቶ በግቢ ውስጥ በመዝራት ማልማት ቀላል ነው፡፡

እባካችሁ አደይ አበባ በመላ አገሪቱ ምን-ምን ይደረግበት እንደሆን፣ እንዴት ያለ ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳለው፣ የመድኃኒትነት ጥቅሙን፣ ወዘተ አጥርታችሁ ጠይቁ፣ አድምጡ፣ የሰማችሁትን ፃፉ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት፡፡

ማጣቀሻ፡-

 1. https://uses.plantnet-project.org/en/Bidens_pilosa_(PROTA)

https://link.springer.com/chapter/10.1007/978-81-322-2163-0_4

 

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

 1. ስለአደይ አበባ በአበበች ቶላ የተጻፈው እንዳለ ሆኖ በተጠቀሰው የሳይንስ ስም ላይ ለውጥ መደረግ አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት በተፈጥሮ የሚበቅለው Bidens prestinaria ነው።

  Bidens boriariana እስከአሁን ከጥቂት ቦታዎችብቻ መተማ ውስጥ (ጎንደር ክፍለ ሃገር) ነው የተገኘው። ሥርጭቱ ከዚያ ተነስቶ በሱዳን በኩል አድርጎ ምእራብ አፍሪካ ሃገሮች በሙሉ እስከ ሴኔጋል እና ጋምቢያ ድረስ፣ በስተሰሜን እስከ ደቡብ ግብጽ ድረስ ነው።

  Bidens pilosa አበባው ነጭ ወይም አበባ የማያወጣ አረም ስለሆነ ለማወቅ አያስቸግርም።

  መስፍን ታደሰ

This site is protected by wp-copyrightpro.com