አባ ጮማ- በተወደደ ሥጋ! (በኪሎ መቶ ሃምሳ ቢሆንስ …!?)

Views: 238

መነሻ፡-

በዓለም ላይ አደንጓሬ ወይም ቦሎቄ የሚባሉት በአጭር ሲገለፁ ነው፡፡ ነገር ግን እጅግ ብዙ ዓይነታት አላቸው፡፡ በብዙ መቶ ዓይነት የሚቆጠሩ ይሆናሉ፡፡  በአንድ ዝርያ ውስጥ በአንድ ሳይንሳዊ ስም የሚጠሩት እራሳቸው እንኳ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ አባጮማ የተባለው ኩላሊት መሣይ ትልልቁ አባÝማ  ወይም ትልቁ ቦሎቄ እንዴት ያለ የጤና ምግብ መሰላችሁ?  በእንግሊዘኛ ስሙ ክሪስማስ ሊማ ቢንስ (Christmas Lima beans ) ይባላል፡፡ በአንዳንድ አገራት ሌሎች ቀለማት እና ሌሎች ዓይነቶቹ በተር ቢንስ (butter beans) ይባላሉ፡፡   በሳይንሳዊ ስሙ ደግሞ ፋስዮሉስ ሉናተስ   (Phaseolus lunatus,) ይባላል፡፡ ፋስዮሉስ ሉናተስ  ተብለው የሚጠሩት እራሳቸው ብዙ ናቸው፡፡ ሊማ ቢንስ የሆኑት ሁሉም ግን በፋስዮሉስ ሉናተስ  ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ሁሉም ሊማ ቢንስ የሚባሉት መገኛቸው ላቲን አሜሪካ ፔሩ ናቸው ይባላል፡፡ ማጣቀሻ አንድ ሁሉም ሊማ ቢንስ በዚህ ዘመን በብዙ የዓለም ዓገራት በሰፊው ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ከብዙ የሊማ ቢን ዓይነታት ውስጥ በእኛ አገር ውስጥ ሰፊ ዕውቅና ያለው ይኸው አባጮማ የተባለው ነው፡፡ እናም በአማርኛ ለግብሩ መገለጫነት ሲባል አባጮማ የተባለው የዛሬው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ተክል በቀላሉ በአጥር ላይ ማልማት ይቻላል፡፡ እነሆ አንብቡ፡፡

ሀ/  አባጮማ ምርታማነቱ

የምርታማነቱ ከፍታ አንድ እግር አባጮማ ሐረግ አንድ ጊዜ በሰፊው አድጎ ሰፈሩን ካለበሰ በኋላ ለአንድ ቤተሰብ በቂ በመሆኑ ነው፡፡ ቦታው ከተመቸው በስድስት ወር ውስጥ ምርት መስጠት ይጀምራል፡፡   አባÝማ በተለምዶ ከአደንጓሬ ዝርያ እንደ አንዱ ተደርጎ ይታሰባል፡፡  ነገር ግን በትክክል የአደንጓሬ ቤተሰብ ይሁን ወይም አይሁን አከራካራ ለጊዜው አከራካሪ አይሆንም፡፡ ብቻ ይህ ሐረግማ ተክል ወይናደጋ በጣም ይመቸዋል፡፡ ደጋ ደግሞ እድገቱ አዝጋሚ ቢሆንም ይመቸዋል፡፡ አበቃቀሉ እንደ ሐረግ ስለሆነ በአጥር ወይም ቆጥ ላይ መንጠላጠል አለበት፡፡ አባÝማ የተባለው ከፍተኛ ምርት ስለሚሰጥ እና ሥጋን ይተካል የሚል ዝና በመያዙ ነው፡፡አንዴ ከተተከለ እስከ አራት ዓመት ድረስ ጥሩ ምርት እየሰጠ ይቆያል፡፡

የሚታወቅባቸው ልዩ ነገሮች አበባው ነጭ፣ ፍሬው የኩላሊት ቅርጽ፣በአንዱ ፍሬ ላይ በአንድ በኩል ቀይ ቡኒ እና በሌላ በኩል ነጭ ስለሆነ በብዛት ሲተይ ቅይጥ ዥጉርጉር ይመስላል፡፡ ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ማለት ነው፡፡ መልካሙ ዜና ይህ እህል ተደጋግሞ ቢዘራም ዓይነቱ ለዘመናት ይኸው ነው፡፡  ይህም ገና ትኩረት ያልተሠጠው ድንቅ የምግብ ዘር ነው፡፡

አባጮማ ፍሬው

እሸት ሣለ የደረሰ ፍሬው ተቀቅሎ እንደ ንፍሮ፣ ወይም እንደ ከሾርባ፣ እንደ ወጥ ወይም ተቀምሞ ከሰለጣ ጋር ይበላል፡፡ ከደረቀ በኋላም ለአንድ ቀን በውሃ ተዘፍዝፎ አድሮ ተቀቅሎ ለተለያየ ምግብ መስሪያ ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ ተከክቶ ገለባው ከወጣለት በኋላ ከስንዴ ጋር ተቀይጦ ይፈጭና ለዳቦ ወይም ለብስኩት ይሆናል፡፡

በብዛት የሚመረተው በወላይታ፣ በወለጋ፣ በከፋ፣ በጂማ እና በሌሎችም ለጊዜው ባልተጠቀሱት አካባቢዎች ጭምር ነው፡፡

እንደሚመረትበት አካባቢ የተለያየ ባሕላዊ ምግብ ይሠራበታል፡፡ ከቆጮ ጋር፣ ከጎመን ጋር፣ ከሌሎች አትክልቶች ጋር ይዘጋጅ እና ይቀርባል፡፡

ለ/ አበቃቀሉ፣

ሐረግማ ስለሆነ እንደአያያዙ በጣም ሰፊ ቦታ ሊወስድ ይችላል፡፡ በትንሽ እና ጠባብ ቦታ ላይ ሐረጉን በመቆጣጠር እዚያው በመጠኑ ምርት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከታች በምስሉ ላይ እንዳለው በዚህ መጠንም ምርት ይሰጣል፡፡

በከተሞች እና በገጠር መንደሮች ጓሮ በቀላሉ ሴቶች፣ህፃናት እና አረጋውያን ሊያለሙት ይችላሉ፡፡

በየማሣው ዳርቻ ባሉ አጥሮች ላይ፣ በአጥር ዙርያ፣ በዛፎች ላይ፣ በቁጥቋጦ እንጨቶች ላይ ተንጠልጣይ ሆኖ እንዲያድግ በማድረግ በብዛት ማምረት ይቻላል፡፡

አባጮማ አነስተኛ ሐረግ

ሐ/ ትልቁ የጤና በረከቱ

በጤና ችግር የተነሳ ሥጋ እንዳትመገቡ የተባሉ ሰዎች ፍሬውን እጅግ ይፈልጉታል፡፡  ለእነሱ በሚስማማ መልኩ ተሠርቶ ሲቀርብላቸው ጥሩ ምግብ ይሆናቸዋል፡፡ ከታች በምስሉ እንደሚታየው የፍሬ ማቀፊያው ረዘም ያለ ነው፡፡ ጮርቃ ሳለ እንዲሁ ከአትክልት ጋር በስሎ ይበላል፡፡ ሲያድግ እና ሲያፈራ ከሁለት እስከ አምስት ፍሬዎች ሊይዝ ይችላል፡፡ ያደገው የፍሬው ማቀፊያ እራሱ ፍሬው ከተሰበሰበ በኋላ ይሰባበር እና ደረቆ ይቀመጣል፡፡ በመጠን ተደርጎ እንደ ሻይ ተፈልቶ፣ ተጠልሎ ይጠጣል፡፡ እንደ አማራጭ የዕፀዋት ሻይ ይሆናል፡፡ በዋናነት ግን ለኩላሊት ጤና ይረዳል፡፡

ከፕሮቲን ይዘቱ በተጨማሪ፤ ለእድገት እና ለሰውነት ቲሹ ጥገና የሚውለው ቫይታሚን ሲ፤ አለው፡፡ ለዓይን ጤና እና ለአጥንት ጤና የሚረዳው ቫይታሚን ኤ አለው፡፡ እንዲሁም መጠነኛ  ማግኒዝየም አለው፡፡ ማጣቀሻ ሁለት፤  

አባጮማ ትንሽ ሐረግ ሳለ

መ/ ዋጋው ስንት ነው

እሸት ሳለ

በሚመረትበት አካባቢ እንዲሁ ተለቅሞ እሸት ሳለ ገበያ ላይ ይሸጣል፡፡ አንድ ኪሎ እርጥቡ ምናልባት ከ1ዐ እስከ 15 ብር ይገኝ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባነሰ ወይም ከፍ ባለ ዋጋም ይሸጥ ይሆናል፡፡

የደረቀው ፍሬው

ከሚመረትበት አካባቢ በምን ያህል ዋጋ እንደተገዛ ለጊዜው መረጃ አልተገኘም፡፡ በአዲስ አበባ ሱፐርማርኬት ውስጥ አንድ ኪሎ አባጮማ ከአንድ እስከ አንድ መቶ ሐምሳ ብር ይገኛል፡፡ ይህ  ተመጣጥኖ ስለሚዘጋጅ እና የጤና ምግብ ስለሆነ ለገዢው (ለተመጋቢው) እጅግ ጥሩ ዋጋ ነው፡፡

ሠ/ ልዩ ጥንቃቄ

መቸም ቢሆን ጥራጥሬ ጥሬውን አይበላም፡፡ አባጮማም ቢሆን ለምግብ ወይም ለመኖ ቢሆን መብሰል አለበት፡፡ በአግባቡ መቀቀል ያስፈልጋል፡፡ ተቀቅሎ ከበሰለ በኋላ ለማንኛውም የምግብ አሠራር ሊውል ይችላል፡፡

ማጠቃለያ:-

አባጮማን አሁን ከሚመረትበት መጠን በብዙ እጥፍ አብዝቶ ማምረት ዕውቀት ነው፡፡

  • ለአገር ውስጥ ተመጋቢ ይሆናል፤
  • በጣሳ ታሽጎ ከውጪ የሚመጣውን ጥራጥሬ ሁሉ ይተካል፣
  • ማንም በመኖሪያ ቤቱ፣ በየትምህርት ቤቶች ጊቢ ሊያለማው ይችላል፤
  • የትም አግባብነት ባላቸው ቦታዎች ሁሉ ማልማት ይቻላል፣
  • በቂ ጥናት ካደረጉ በኋላ በሰፊው ቢያመርቱት ድንቅ ሥራ ነው፡፡

የአባጮማ አቻ ተክል በቆላ ምድር የሚለማው ጃክ ቢን ነው፡፡ ማጣቀሻ ሶስት፤   በዘልማድ ሁለቱንም  ቦሎቄ  ወይም አባጮማን የወይናደጋ ቦሎቄ፣ ጃክ ቢን የቆላ ቦሎቄ እንላለን፡፡ ነገር ግን በዝርያ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው፡፡ የሚያመሳስላቸው  ሐረግ መሆን እና ጥራጥሬ መሆናቸው ነው፡፡

                                                            ጥራጥሬን በአግባብ ተመገቡ፡፡

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ፤   https://happyacres.blog/2016/01/19/featured-cooking-bean-christmas-lima/

ማጣቀሻ ሁለት    https://www.google.com/search?q=chritmas+lima+beans+helath+benefit&ie

ማጣቀሻ ሶስት፤   https://ethio-online.com/archives/2881

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com