ቅምሻ ከወዲያ ማዶ፡- አሜሪካ በምርጫዬ ላይ ሩሲያ፣ ቻይና እና ኢራን ጫና ለማሳደር ይጥራሉ አለች

Views: 50

ቻይና፣ ሩሲያ እና ኢራን በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጫና ለማሳደር ከሚጥሩ አገራት መካከል ዋነኛዎቹ መሆናቸውን አንድ የአሜሪካ ደህንነት ኃላፊ አስጠነቀቁ።

የአሜሪካው ፀረ ስለላ ዳይሬክተር ባወጡት መግለጫ ላይ የውጪ አገራት ኃይሎች ‘ድብቅ እና ግልጽ ጫና ማሳደሪያ መንገዶችን’ እየተጠቀሙ የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ነው ብለዋል።

የአሜሪካው የብሄራዊ ፀረ ስለላ እና ደህንነት ማዕከል ዋነኛ ኃላፊነት የአሜሪካን የስላል ፕሮግራም ከተቀናቃኝ አገራት መጠበቅ ነው። በጽሑፍ የወጣው መግለጫ ቻይና፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ በስልጣን እንዲቆዩ አትፈልግም።

ሩሲያ ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑት ጆ ባይደንን ለመጉዳት ትፈልጋለች። ኢራን በበኩሏ አሜሪካውያን በዲሞክራሲያዊ ስርዓታቸው እምነት እንዲያጡ ዓላማዋ ነው ሲል ይኮንናል።

ከ4 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2016 ፕሬዝደንት ትራምፕን ወደ ስልጣን ያመጣው ምርጫ ላይ ሩሲያ እጇን አስገብታ ነበር ሲሉ የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ይከሳሉ።

የደህንነት ባለስልጣናቱ ሩሲያ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ጭምር ለትራምፕ ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጉልበት ሰጥታለች ይላሉ። ሩሲያ ግን ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላት በተደጋጋሚ አስታውቃለች።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ትናንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሕዳር ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይ የውጪ ኃይሎች ተጽእኖን ሪፖርትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ አስተዳደራቸው “ጉዳዩን በጣም በቅርብት እየተከታተለ ነው” ብለዋል።

ይህ በአሜሪካ ምርጫ ላይ የውጪ ኃይሎች ፍላጎት የተሰማው ፕሬዝደንት ትራምፕ ምርጫው ይራዘም ሲሉ አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ ነው። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በፖስታ የሚደረገው ምርጫ ተዓማኒነት ጥያቄ ያስነሳል በሚል ነበር ትራምፕ ምርጫው ይራዘም የሚል ሃሳብ ያቀረቡት።

ይህ ሃሳባቸው ግን ከፓርቲያቸው ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎባቸዋል።

የብሄራዊ ‘ካውንተር ኢንተለጀንስ’ እና ደህንነት ማዕከል ዳይሬክተር ዊሊያም ኢቫኒና ትናንት ባወጡት መግለጫ ላይ የውጪ ኃይሎች በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤት ላይ ጫና የማሳደር ፍላጎት እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።

ዳይሬክተሩ፤ የውጪ አገራት ዓላማ የድምጽ ሰጪዎችን ፍላጎት እና የአሜሪካን ፖሊሲ ማስቀየር ከዚያም የአሜሪካ ህዝብ በአገራቸው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ እምነት ማሳጣት ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የውጪ ኃይሎቹ ይህን ፍላጎታቸውን እውን ማድረግ እንደማይቻላቸው በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

እጃቸውን በአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለማስገባት ፍላጎት ያላቸው አገራት ዋነኛ ፍላጎት ምርጫውን ማን ያሸንፋል የሚለው ላይ መሆኑን እና የቻይና፣ ሩሲያ እና ኢራን ጣልቃ ገብነት እንደሚያሳስባቸው ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ቻይና፤ “ፕሬዝደንት ትራምፕ ምርጫውን እንዲያሸንፉ አተፈልግም” የሚለው መግለጫው፤ ‘በቀጣይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የማይገመቱት ፕሬዝደንት ትራምፕ’ ዳግም በዋይት ሃውስ ለአራት ዓመታት እንዲቆዩ ቻይና አትፈልግም ሲል ይኮንናል።

ሩሲያ የትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑትን ጆ ባይደንን ‘መጉዳት’ ትፈልጋለች ይላል የፀረ ስለላው መግለጫ። በተጨማሪም ‘ጸረ-ሩሲያ’ የሆኑ ተቋማት በሩሲያ ኢላማ ውስጥ ገብተዋል።

ኢራን በበኩሏ “የአሜሪካን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ለማሳጣት” እና “ፀረ አሜሪካ የሆኑ ሃሰተኛ መረጃዎችን በኢንተርኔት በማሰራጨት አገሪቱን ለመከፋፈል” ፍላጎት አላት ይላል መግለጫው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com