ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) የእነ አቶ ጃዋር የፍርድ ቤት ውሎ

Views: 59

ከፍተኛ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እና አባላትን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ትናንት ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ከተጠርጣሪ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ፍርድ ቤት የቀረቡት በኮሎኔል ገመቹ አያና መዝገብ ሥር የተካተቱ 11 ተጠርጣሪዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች እና አማካሪዎች ኮሎኔል ገመቹ አያና፣ ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)፣ ሚካኤል ቦረን እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይገኙበታል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ፤ የሰው ነብስ እንዲጠፋ፣ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ መንግድ እንዲዘጋ እና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቆም አድርገዋል ሲል ጠርጥሬያቸዋለሁ ስለማለቱ ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሥማቸውን ከላይ የተጠቀሰው የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንድ ወር ቢያልፋቸውም፤ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን እና ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸውም ጋር ግነኙነት እንዳልነበራቸው ጠበቃ ቶኩማ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቆ፤ የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ማቆያ እንዲያመሩ መጠየቁን ጠበቃ ቶኩማ አሳውቀዋል።

ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ግን ክስ የማይመሰረት ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሰው ጊዜ ፍርድ ቤት መምጣት ሳያስፈልጋቸው ከእስር ይውጡ ብሎ በማዘዝ የመርመራ መዝገቡ መዘጋቱን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ የተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ከዚህ በፊት አግኝተው እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ በመናገር፤ ደንበኞቻቸው ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ መብታቸውን የሚጠብቅ አለመሆኑን እና ለችግር ተዳርገው እንደሚገኙ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።

በተለይ የስኳር እና ደም ግፊት ሕመሞች ተጠቂ የሆኑ ተጠርጣሪዎች የሚወስዷቸውን መድሃኒቶች ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠበቃው ለፍርድ ቤት ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮሎኔል ገመቹ አያና ታስረው የሚገኙበት ስፍራ በቂ የጸሃይ ብርሃን እንደሌለው እንዲሁም በቂ ምግብ እያገኙ አለመሆኑን በመጥቅስ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

ጠበቃው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቱ የታሳሪዎች አያያዝ መብት እንዲከበር፤ መድሃኒት የሚያስፈልጋቸውም መድሃኒት እንዲቀርብላቸው፣ ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማዘዙን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ጫልቱ ታከለ ትናንት የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረቧን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል። የኦነግ አባል የሆነችው ጫልቱ ታከለ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ የአራዳው ምድብ ችሎት በ4 ሺህ ብር የዋስ መብት ከእስር እንድትወጣ ካዘዘ በኋላ፤ ጫልቱ ዳግም በኦሮሚያ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውላ ወደ ሱሉልታ መወሰዷ ይታወሳል።

በትናንቱ ውሎ መርማሪ ፖሊስ ጫልቱ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት ግን ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ በማድረግ በከዚህ ቀደሙ የዋስትና መብት ከእስር ትውጣ በማለት ማዘዙን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌሎች በሱሉልታ ተይዘው የሚገኙት የኦነግ መካከለኛ አመራር የሆኑት ለሚ ቤኛ እና ዳዊት አብደታ በተለያዩ ምክንያቶች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ትናንት ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ኬኒያዊውን ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ጨምሮ 11 ሰዎች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር ይለቀቁ ሲል መበየኑን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አብዱለጢፍ አሜ ኤሌሞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ ያሲን ጁማን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች ሐምሌ 29 የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቅ ከእስር ሳይለቀቁ ቆይተው ነበር።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን እንዲያሰማ ፈቅዷል።

የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥም ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ይህ ውሳኔ የሰጠው ተጠርጣሪዎች እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 ፍርድ ቤት በቀረቡብት ወቅት ነበር።

በዚህ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ውስጥ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አደን (ቦረና)፣ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ፣ የዓለምወርቅ አሳ፣ ጌቱ ቱዳ፣ ሸምሰዲን ጣሃን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ሰዎች ተካትተዋል።

ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 በተካሄደው የችሎት ውሎ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ናቸው ከተባሉ 15 ግለሰቦች መካከል 5 ሰዎች በዐቃቤ ሕግ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑ ተነግሯል።

እነዚህ 5 ሰዎች ማንነታቸው ሳይጠቀስ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።ለመሆኑ ቀዳሚ ምርመራ ምንድነው?
የሕግ አማካሪ እና ጠበቃው አቶ ታምራት ኪዳነማርያም በቅድሚያ አንድ ሰው ተጠርጥሮ ከተያዘ አንስቶ ብይን እስከሚሰጥበት ድረስ ያለውን የሕግ አካሄድ ያስረዳሉ።

“አንድን ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ የሚይዘው ፖሊስ ነው። የወንጀል ምርመራው የሚያጣራው ደግሞ በፖሊስ ውስጥ ያለው ምርመራ አጣሪ ክፍሉ ነው” ይላሉ አቶ ታምራት።

ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለውን ግለሰብ ቃል ይቀበላል። አስፈላጊ ከሆነ ተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት ይቆያል። ተጠርጣሪውን ማሰር ሳያስፈልግ ምርመራውን ማካሄድ የሚቻል ከሆነ ግን፤ “ተጠርጣሪው ቃሉን ሰጥቶ፣ ዋስ ጠርቶ ወደ ቤቱ ሊሄድ ይችላል” ይላሉ።አንድ ተጠርጣሪ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ከተደረገ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚኖርበት የሚያስታውሱት አቶ ታምራት፤ ፍርድ ቤትም ለመርማሪ ፖሊስ እስከ 14 ቀናት የሚረዝም የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል ይናገራሉ።

“ፍርድ ቤት ሊፈቅድ የሚችለው የምርመራ ጊዜ ቢበዛ 14 ቀናት ናቸው” የሚሉት አቶ ታምራት፤ የግድ ግን ፍርድ ቤት የሚፈቅደው 14 ቀናት እንዳልሆነ ያሳስባሉ። “3 ቀን ሊሆን ይችላል፣ 1 ቀን ሊሆን ይችላል። ፍርድ ቤት ይበቃል ብሎ የሚያምነው ጊዜ ይሰጣል” ይላሉ።

ፖሊስ በተደጋጋሚ ምን ያክል ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት መጠየቅ ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “እሱ ሕጋችን ላይ ክፍተት አለው። ፖሊስ እየደጋገመ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ይችላል። ፍርድ ቤት ግን የፖሊስን ጥያቄ የመቀበል ሕጋዊ ግዴታ የለበትም። እንደውም የፖሊስን ጥያቄ መርምሮ ካላመነበት አለመቀበል ይጠበቅበታል” ይላሉ።

የፖሊስ የምርመራ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ወደ ዐቃቤ ሕግ እንደሚያመራ እና ዐቃቤ ሕግ ሶስት ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል አቶ ታምራት ያስረዳሉ።

“የፖሊስ ምርመራ ሲጠናቀቅ ጉዳዩ ወደ ዐቃቤ ሕግ ያመራል። ምርመራው በተጠናቀቀ 15 ቀናት ውስጥ ክስ ሊመሰርት ይችላል። ወይም የተሰበሰበው ማስረጃ በቂ ካልሆነ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ሊወስን ይችላል። አልያም ደግሞ የተሰበሰበው ማስረጃ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስለመፈጸሙ የሚያመላክት ነገር ከሌለበት ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪውን በነጻ ሊያሰናብተው ይችላል” ሲሉ ያብራራሉ።

ቀዳሚ ምርመራ በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ያለ መሆኑን በመጥቀስም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ እንጂ በአሁኑ ወቅት ብዙ ጊዜ ሥራ ላይ ሲውል እንደማይታይ አቶ ታምራት ይናገራሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com