ቅምሻ ከወዲያ ማዶ፡- የሳዑዲ እረጅም እጅ ጉዞ

Views: 53

የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ቅጥረኞቻቸውን ወደ ካናዳ በመላክ የቀድሞ የሳዑዲ የደህንነት ቢሮ ባለሥልጣናንን ለመግደል አሲረዋል ተብለው ተወነጀሉ። የከሸፈው ዕቅድ ዓላማ ሳድ አል-ጃብሪን መግደል ነበር ተብሏል።

የልዑል ቅጥረኛ ገዳዮች ይህን ለመፈፀም ወደ ካናዳ ያመሩት ከጃማል ኻሾግጂ ግድያ በኋላ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ተናግሯል።

የሳዑዲ ደህንነት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን የነበሩት ጃብሪ ሃገራቸውን ጥለው ወደ ካናዳ የኮበለሉት ከሶስት ዓመታት በፊት ነበር።

ሰውዬው ቶሮንቶ ውስጥ ጥብቅ ጥበቃ በሚደርግለት መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። ፍርድ ቤቱ እንደሚለው ግድያው ላይሳካ የቻለው የካናዳ ድንበር ጠባቂዎች ቅጥረኛ ገዳዮቹ የቶሮንቶ ፒርሰን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን አልፈ ሊሄዱ ሲሉ በጥርጣሬ ስለመለሷቸው ነው።

የ61 ዓመቱ ጃብሪ ለዓመታት በብሪታኒያው ኤም አይ 6 እንዲሁም ሌሎች ምዕራባውያን የስለላ ድርጅቶችና በሳዑዲ መካከል ያለውን ግንኙነት ሲመራ የነበረ ሰው ነው ተብሏል።

106 ገፅ ያሉት ዋሽንግተን ዲሲ ላለ ፍርድ ቤት የቀረበው ያልተረጋገጠ ክስ ልዑሉ፤ የጃብሪን ድምፅ ለማፈን ሲሉ ሊገድሉት አሲረዋል ሲል ይወነጅላል።

ጃብሪ፤ ይህ ከሽፏል የተባለው ግድያ የታቀደለት ‘ከባድ ምስጢር’ በመያዙ እንደሆነ ይናገራል። ክሱ እንደሚያመለክተው ጃብሪ ከያዛቸው ምስጢሮች መካከል የባለሥልጣናት ሙስና ቅሌትና ‘ታይገር ስኳድ’ በመባል የሚታወቀው የቅጥረኛ ገዳዮች ቡድን መረጃ ነው።

‘የታይገር ስኳድ’ አባላት በፈረንጆቹ 2018 ቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ የተገደለው ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂን ግድያ በማቀነባበር ይወነጀላሉ።

ክሱ እንደሚለው ልዑሉ፤ ሳድ አል-ጃብሪን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የፈለጉት ሰውዬው በጣም በርካታ የሳዑዲ ባለሥልጣናትን ምስጢር ስለሚያውቁ ነው።

ሳድ አል-ጃብሪ ልዑል አልጋ ወራሹ 2017 ላይ ካደረጉት ሹም ሽር በፊት ነው በቱርክ በኩል አድርገው ወደ ካናዳ የሸሹት።

አል-ጃብሪ፤ “ልዑል አልጋ ወራሹ በተደጋጋሚ ወደ ሳዑዲ እንዲመለስ ሙከራ አድርገዋል፤ ሌላው ቀርቶ ‘ልናገኝህ ይገባል’ የሚል የጽሑፍ መልዕክት ልከውልኛል” ይላል።

ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው የጃማል ኻሾግጂን ሰውነት በመገነጣጠል የተጠረጠረው ግለሰብ ለሬሳ ምርመራ የሚሆኑ መሣሪያዎች በሁለት ቦርሳዎች ይዞ ነበር ወደ ካናዳ ለመግባት የሞከረው።

ነገር ግን የካናዳ ድንበር ጥበቃ ሰዎች የቡድኑ አባላት ላይ ጥርጣሬ በማሳደራቸው እንዳይገቡ ከለከሏቸው ይላል ክሱ።

የሳዑዲ መንግሥት ስለ ክሱ እስካሁን ምንም ያለው ነገር ይለም።

የካናዳ ሕዝብ ደህንነት ኃላፊ ቢል ብሌይርም በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ነገር ግን መንግሥት አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ካናዳ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ እንደሆነ ያውቃል ብለዋል።

ሳድ አል-ጃብሪ ለዓመታት የልዑል ሞሐመድ ቢን ናይፍ ቀኝ እጅ ነበር። አል-ቃኢዳ ወደ ሳዑዲ ዘልቆ እንዳይገባ በመመከትም ይሞገሳል። ሳዑዲ ከዩናይትስ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ኒው ዚላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት በመምራትም ይታወቃል።

ከኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ በሰው ሰራሽ ልህቀት የዶክትሬት ድግሪ ያለው ሳድ አል-ጃብሪ ድምፁ ብዙም የማይሰማ የደህንነት ሰው ነው ይባልለታል። ሰውዬው በሃገር ውስጥ ሚኒስቴር የሜጀር ጄኔራል ማዕረግ መድረስ ችሏል።

ነገር ግን፣ በፈረንጆቹ 2015 ንጉስ አብዱላህ ሞተው ወንድማቸው ሳልማን ወደ መንበሩ በመምጣት ወጣቱ ልጃቸው ቢን ሳልማንን መከላከያ ሚኒስቴር አድርገው ሲሾሙ ሁሉም ነገር ተቀያየረ።

በእንግሊዝኛው ምሕፃረ ቃል ኤምቢኤስ በመባል የሚታወቁት ቢን ሳልማን ደም አልባ መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ቤተ መንግሥቱን ሲቆጣጠሩ ነው ጃብሪ ከሃገር ሸሽቶ ወደ ካናዳ የገባው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com