ያልተዜመለት የእህል አባት- ዳጉሳ!

Views: 285

መግቢያ፡-

በአምራቶቹ ዘንድ፣ ዳጉሳ (ደጉሳ)- የእህል አባት፣ ገብስ- የእህል ንጉስ፣ ጤፍ- የእህል እናት፣ ማሽላ- የእህል አውራ፣ አደንጓሬ- የእህል አውሬ፣ ይባላል፡፡

ዳጉሳ ለምን የእህል አባት የሚል ትልቅ ስም እያለው ብዙ ጠቀሜታ ሳይሰጥ ቀረ? ቢባል፤  ጥያቄ እና ምርምሩን ቀጥሉበት፡፡ ለዛሬው ግን ስለ ዳጉሳ መነሻ ሐሳብ ቀጥሎ ያለውን አንብቡ፡፡

የአማርኛ ስሙ የተገኘው ከብቃቱ ነው ይባላል፡፡ ደጉ፣ መልካሙ፣ ምቹ፣ እንደ ማለት ሆኖ ደጉ ከሚለው ቃል ወደ ደጉሳ፤ ቀጥሎም ዳጉሳ ተባለ ይላሉ አምራቾቹ፡፡

ዳጉሳ በእንግሊዘኛ ፊንገር ሚሌት /Finger millet/ በሣይንሳዊ አጠራሩ ኢሉሲኔ ኮራካና፣(Eleusine coracana) ይባላል፡፡ በአገረ ህንድ ኩራካና ሚሌት /kurrakan millet/ ወይም ኮራካና ሚሌት /koracan millet/፣  ራጂ /ragi/ ወይም ናችኒ /nachni/  ተብሎ ይጠራል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ያፍሪካ ሚሌት /African millet/፣ ወይም ራፖኮ /rapoko/ ይባላል፡፡

ዳጉሳ በኦሮሚፋ ዳጉጃ (Daagujja)፣ በትግርኛ  ዳጉሻ፣ ሲሆን ነጭ ዳጉሳ /ፀአዳ ዳጉሻ/፣ ጥቁር ዳጉሳ  /ፀሊም ዳጉሻ/ ይባላል፡፡

ምስል ሁለት፣ የዳጉሳ የዘለላው ምስል

አንደኛ ነገር/ የዳጉሳ ጉዳይ

ዳጉሣ (የእህል አባት) በወይና ደጋ እና እርጥብ ቆላማ ማሽላ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ይበቅላል፡፡ በአንድ የምርት ወቅት የሚዘመር የእህል ዘር ሲሆን፣ አበቃቀሉ የአክርማ ሣር ይመስላል፡፡ የሚያፈራው አናቱ ላይ እንደ ጣት በተዘረጉት መስመሮች ውስጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በጣም የታወቁት ነጭ፣ ቀይ፣ ቀይ ቡኒ እና ጥቁር ወይም ቀይ እና ነጭ ቅይጥ የዳጉሳ ዓይነቴዎች አሉ፡፡

ነጩ በገበያ ላይ በብዛት አይገኝም፡፡ ነጩ ምናልባትም በብዛት የሚገኘው በትግራይ ቆላማ አካባቢዎች እና በባሕርዳር ዙሪያ ይሆናል፡፡ በአነስተኛ መጠን በሰሜን ጎንደር አዲአርቃ ወረዳ ወይም ፀለምት ውስጥ ይሆናል፡፡  ቀዩ ወይም ቀይ ቡኒው በብዛት የሚገኘው በጎጃም፣ በወለጋ እና  በሻሸመኔ ዙሪያ ነው፡፡

ምስል ሶስት፣ የዳጉሳ ዘር፣ በግራ ነጭ፣ በቀኝ ጥቁር ቡኒ ዓይነት

የአፍሪካ ነባር ዝርያ የሆነው ዳጉሳ ቀደምት መገኛው (መነሻው)  ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ከፍተኛ ቦታዎች ናቸው፡፡  ነገር ግን ምግብነቱ በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሰጠው፤ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ በቤት ውስጥ ለሚዘጋጁ ባህላዊ መጠጦች ማዘጋጃ የተተወ ነው፡፡ ዳጉሳ ከማንኛውም ዋናዋና የዓለም የእህል ምርቶች እጅግ በንጥረ ምግብ ይዘቱ የዳበረ ነው፡፡

ዳጉሳ ድርቅን በእጅጉ መቋቋም ይችላል፡፡ ከአምስት አመታት በፊት በ2ዐዐ7 ዓ.ም በተከሰተው የዝናብ እጥረት በተዘራበት አካባቢ ሌሎች ሰብሎች (እንደ በቆሎ ያሉ) ጠውልገው እና ቀጭጨው ሳለ፣ ዳጉሳ ልምላሜውን እንደጠበቀ ነበር፡፡ ለምሳሌ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በሻሸመኔ ዙሪያ ባሉት ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ የነበረው የዳጉሳ ልምላሜ ልዩ ነበር፡፡

ሁለተኛ ነገር/ የዳጉሳ ሥነ ምግብ ይዘት

ዳጉሳ እጅግ ጠቃሚ ምግብ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ትኩረትም የኸው የምግብነት ይዘቱ ትኩረት አግኝቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና ለህብረተሰባችን የምግብ ዋስትና የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለመጎትጎት ነው። የካልስየም እና ብረት ማዕድን ይዘቱ ከጤፍ እጅግ ይበልጣል፡፡ በካልሲየምና ብረት ማዕድን ይዘት የበለጸገ እህል ሲፈለግ በቅድሚያ የሚጠቀሰው ጤፍ ነው። ነገር ግን “ጤፍ በካልስየም እና ብረት የበለፀገ ነው” የሚሉት የዳጉሳን ይዘት ያላወቁ ናቸው፡፡

በሚበቅልበት አካባቢ ዳጉሳን ለእንጀራ ይጠቀሙታል፡፡ ነገር ግን በማይለማበት አካባቢ በተለይም በከተሞች ዳጉሣ ታዋቂነትን ያተረፈው ለጠላና ካቲካላ አረቄ ማዘጋጃነት በመዋሉ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ያለ በቂ ምክንያት ከዋና ምግብነት ተርታ ተገፍቶ ተለየ እንጂ  ጠቃሚ ምግብ ነው፡፡

በአዘገጃጀትም ቢሆን፣ ዳጉሳ ለእንጀራ፣ ለዳቦ፣ ለብስኩት፣ ለኩኪስ፣ ለቂጣ እና ለተለያዩ በሀገራችን የተለመዱ ምግቦች እና መጠጦት ዝግጅት ሊውል ይችላል፡

ዳጉሳ እጅግ የዳበረ ንጥረ ምግብ ይዘት እንዳለው ከ4ዐ አመታት በፊት በኢትዮጵያ የተካሄደው ጥናት በሰፊው ያስረዳል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ሰንጠረዥ ከዚሁ ጥናት መጽሔት ላይ ተወስዶ በ “ሕክምና በቤታችን፤ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት”  መጽሐፍ ላይ ከተፃፈው የተወሰደ ነው፡፡

የመረጃ ምንጭ፣ የሥርዓተ ምግብ ትምህርት 2ኛ መጽሐፍ፣ 1973 ዓም፣ የኢትዮጵያ ምግብ ጥናት ድርጅት፣ አዲስ አበባ
ከሰንጠረዡ ላይ በሚታየው መረጃ መሠረት፤ የዳጉሳ የምግብ ሐይል እና ካርቦሃድሬት ከሌሎች ሰብሎች ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡ ነገር ግን በካልስየም እና በብረት ይዘቱ ልቆ ይገኛል፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ የሥር ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከቱ፡፡

ሶስተኛ ነገር/   የዳጉሳ አይበገሬነት

ሌላው የዳጉሳ ልዩ ብቃት በተባይ የማይደፈር መሆኑ ነው። ምንም የኬሚካል ማቆያ ሳይደረግበት ለብዙ አመታት መቆየት ይችላል፡፡ አምራቾቹ  “ዳጉሣ ለብዙ ዓመታት ለምሣሌ እስከ 1ዐ አመታት ቢቀመጥ አይነቅዝም፡፡ በቶሎ የሚነቅዙ የእህል ዘሮች ሣይነቅዙ እንዲቆዩ ከዳጉሣ ጋር ተቀይጠው ቢቀመጡ ለአንድ በጋ ከመንቀዝ ይድናሉ ”  በማለትም ያብራራሉ፡፡

የዳጉሳ አይበገሬነት በብዙ ምሳሌ ይገለፃል፡፡ በእህል ውድማ ላይ እየተወቃ ሳለ፣ ተበራይቶ ሳይጠናቀቅ ወይም ተበጥሮ ሳይጠናቀቅ ከፍተኛ ዝናብ ቢወርድበት፣ ከላይ ያለው ይበቅላል፣ ከሥር ላለው ሽፋን ይሆናል፡፡ ገበሬው የዝናቡ ሳምንት ካለፈ በኋላ፣ ከላይ  እንደልባስ ያለውን የዳጉሳ ብቃይ ገፎት ያነሳዋል፡፡ ከሥር ያለውን በውሃ ያልተነካ የዳጉሳ እህል አበጥሮ ይወስደዋል፡፡

ይህ ዓይነት ፀባዩ ጎልቶ በሚወራበት አዲአርቃይ እና ፀለምት አካባቢ ዜናው ከዚህም በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ከ2ዐ አመታት በፊት “አንድ ክረምት እንኳን ቆይቶ ከሥር ያለው አይበላሽም”  የሚሉ አርሶ አደሮች ነበሩ፡፡

“በውድማ ላይ እየወቃን ሳለ የጦርነት መከራ ሲያጋጥምን፣ እዚያው ከምረን እንሄዳለን፤ ከወራት በኋላ አካባቢው ሲረጋጋ ተመልሰን ከላይ ያለውን አንስተን የዳጉሳ እህል ከሥር እናገኛለን፡፡” በማለት የነገሩኝ የፀለምት አርሶ አደሮች ነበሩ፡፡

አራተኛ ነገር/  ሌሎች ልዩ ብቃቱ

ስለ ዳጉሳ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO)፣ የሚከተለውን ይነግረናል፡፡

ልዩ ብቃቱ

  • ግሉቲን የሌለው መሆኑ፣
  • ከፍተኛ ካልስየም እና አይረን በመያዙ፣
  • ግሩም የሆነ ብቅለት ስላለው በምግብ ማቀነባበር ውስጥ ያለው ጠቀሜታ መጨመሩ፣

ለአነስተኛ እርሻ ባለቤቶች ያለው ጠቀሜታ

  • ሰብልን አፈራርቆ  ከበቆሎ፣ማሽላ እና/ወይም ጥራጥሬ ጋር/፤ለመዝራት ይውላል
  • በአነስተኛ ግብዓት በቂ ምርት ይገኝበታል፤
  • ዝቅተኛ የአፈር ልምላሜ ባለው መሬት ላይ ምርት ይሰጣል፡፡

የመረጃ ምንጭ    Food and Agriculture Organization of the United Nations Traditional Crop of the Month

በህንድ አገር የሚገኘው ኖሪሽንግ ዘ ፕላኔት፤  Finger Millet: A Once and Future Staple

በሚል  ርዕስ  አዘጋጅቶ በ ማት ስቲስሊንገር (Matt Styslinger) በመረጀ መረብ የተለቀቀው ፅሑፍ ዳጉሳን እንዲህ እንደሚከተለው  ገልፆት ነበር፡፡

ዳጉሳ የእስታርች ይዘቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከስንዴ በበለጠ ፕሮቲኑ በቀላሉ ሆድ ውስጥ ይብላላል፡፡ ዳጉሳ በዓለም ከማንኛውም የእህል ዓይነት በብረት ማዕድን ይዞታው፣ ከአማራንዝ (ካቲላ) እና ኪኑዋ ቀጥሎ 3ኛ ነው፡፡ በኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን የሚገኙ ጥቂት የዳጉሳ ዓይነቴዎች፤ ከፍተኛ ሜቲዮኒን የተባለ አሚኖ አሲድ /methionine, an amino acid /አላቸው፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ ሚሊየን በሚቆጠሩ ደሃ ህዝቦች፣ በተለይም የእስታርች ምግብ እንደ ካዛቫ ካለ ሥራሥር በዋናነት የሚመገቡት ዘንድ ይህ አሚኖ አሲድ እጥረት አለ፡፡ በ ምግብ አሠራር ረገድም በሰሜን አፍሪካ ቱዋ ዛፊ /tuo zaafi/  የተባለ ገንፎ፤ በሳሃራ አገራት  ደግሞ ታጉሌ /taguella/ የተባለ የዳጉሳ ዳቦ፣ ይጋገራል፡፡

ዳጉሳ በደረቅ አካባቢዎች ተመራጭ እህል ነው፤ ምክንያቱም ውሃ ሳያገኝ ቢቀር እንኳን ለሳምንታት ሳያድግ ዝም ብሎ ተቋቁሞ ይቆይና ዝናብ ባገኘ ጊዜ መብቅል እና ማደግ ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም እንደ ዝርያው ሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርት ይሰጣል፡፡

እስከ ቅርብ አስርተ አመታት በአፍሪካ የታወቀ ሰብል ቢሆንም፣ በቅርቡ የዳጉሳ ምርት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ዳጉሳ በሚመረትባቸው አገራት በብዙ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ (የደሃ ምግብ) እየተባለ፣ እንዲሁም በሳይንሱ ማህበረሰብ ዘንድ ምንም ትኩረት ያልተሰጠው ነው፡፡ ብዙ አርሶ አደሮችም ሥራው እጅግ አድካሚ በመሆኑ ተስፋ በመቁረጥ ከዳጉሳ ይልቅ በቆሎ፣ ማሽላ እና ካዛቫ ማምርትን የሚመርጡ በመሆኑ ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

አምስተኛ ነገር/  ዳጉሣ በኢትዮጵያ ለእንጀራ 

 “በዐይነት እንጀራ ለምለም እንጀራ ከብዝሀ ሰብሎች”  በሚለው መጽሐፍ ላይ ከተገለፀው እንደሚከተለው በአጭሩ ተወስዷል፡፡

የዝግጅት ሂደት

ከጤፍ ወይም ከሌላ የተለመዱ የእህል አይነቶች ጋር የተደባለቀ ጥሩ የዳጉሳ እንጀራ ለመጋገር የሚከተሉትን የአሰራር ሂደቶች መከተል፤

ዳጉሣው በገለባ የተሸፈነ ከሆነ መሸክሸክና ማበጠር ከዚያም ማጠብ እና  በፀሐይ ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ከሚፈለገው እህል ጋር አመጣጥኖ ቀይጦ ማስፈጨት ነው፡፡ ቀዩን ዳጉሣ ከቀይ ጤፍ ጋር፣ ከገብስ ጋር፣ ካሳቫ ኮረት ጋር ወይም ከጎደሬ ኮረት ጋር አደባልቆ ማስፈጨት ነው፡፡

ምስል አራት፣ ቀይ ዳጉሳ እህል

የእንጀራው ዓይነት

የቀይ ዳጉሣ እንጀራ  እንደ ቀይ ጤፍ ዓይነት ነው፡፡ ዓይኑ እና ሰበከቱ ያማረ ነው፡፡ ከቀይ ጤፍ ጋር ሲቀየጥ ደግሞ ጥሩ ይሆናል፡፡ የንጥረ ምግብ ይዘቱ በተለይ በካልስየም ከጤፍ ይበልጣል፡፡  በጣም ሣይቦካ በአፍለኛነቱ ተጋግሮ  ቢመገቡት የበለጠ ጥሩ ነው፡፡

ምስል አምስት፣ ቀይ ጤፍ እና ቀይ ዳጉሳ ተመጥኖ

አፍለኛው እንጀራ በድርብ ተዘጋጅቶ

  ዳጉሣ ምግብ ከተዘጋጀ በኋላ የንጥረ ምግብ ይዘቱ

በመቶ ግራም የዳጉሣ እንጀራ፣ የዳጉሣ ዳቦ እና የቀይ ጤፍ እንጀራ ውስጥ ያለ የንጥረ ምግብ ይዘት በዐይነት እንጀራ መጽሐፍ ላይ እንደቀረበው

የመረጃ ምንጭ፡ የኢትዮጵያ የጤናና ስነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት፡

FOOD COMPOSITION TABLE FOR USE IN ETHIOPIA:

ስድስተኛ ነገር/ ዳጉሳ እንደ መድኃኒት

ከህክምና በቤታችን መጽሐፍ ላይ የተወሰደ

ዳጉሳ ለደም ማነስ

ዳጉሳ እጅግ ከፍተኛ የብረት እና የካልስየም ማዕድን  በመያዙ ለደም ማነስ ታማሚ የሚረዳ ነው፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ጠቃሚ እህል/ጥራጥሬ ጋር ለምሳሌ ከቀይ ጤፍ፣ ጓያ፣ ምስር፣ እና አኩሪአተር ጋር ተመጣጥኖ ከተፈጨ በኋላ በሚፈልጉት የምግብ አሠሪር አዘጋጅቶ መጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ለአጥሚት፣ ለህፃናት ገንፎ፣ ለቂጣ፣ የተሠበረ ሰው ለማስታመም ወዘተ፡፡

የዳጉሳ ጭምቆ  ለወባ በሽታ

የወባ ሕመም በሰውነት ውስጥ ብዙ ሲቆይ ጣፊያ ያሳብጣል፡፡ ይህንን የሆድ እብጠት በአንዳንድ አካባቢ “ቋጓ ሠራ” ወይም “መጅ ሠራ” ይሉታል፡፡ በወባ የታመመ ሰው ቋጓ ወይም መጅ እንዳይፈጠርበት ቀድሞውኑ ጭምቆን በማር እየመታ ጠዋት ማታ አንድ ብርጭቆ ይጠጣል፡፡ ጭምቆ ከዳጉሳ የሚዘጋጅ መጠጥ ነው፡፡

አዘገጃጀቱ እንዲህ ነው፡፡ የዳጉሳ ዱቄት ተቦክቶ በ3ኛው ቀን ይጋገርና በጌሾ እና ብቅል ይጠነሰሳል፡፡ ቀጥሎ ለአንድ ሳምንት በየቀኑ ቡኮው እየወጣ ይታሻል፤ ዕቃው እየታጠነ የታሸው ተመልሶበት ይከደንና ይቀመጣል፡፡ ከ አንድ ሳምንት በኋላ ሌላ የዳጉሳ ዱቄት ቂጣ ተጋግሮ ወድያው ይገባል፡፡ ከ 3 ቀን በኋላ ድፍድፉ ትንሽ ውሃ ተጨምሮበት ይጨመቃል፡፡ በወፍራሙ ማለት ነው፡፡ ይህ ነው ጭምቆ ማለት፡፡ ይህ አሠራር በአንዳንድ ቦታ የጠላ አጠማመቅ ስልት ነው፡፡ ብዙ ውሃ ገብቶበት ከተጨመቀ ጠላ ይባላል፡፡ ለተጐዳ ሰው በወፍራሙ ሲዘጋጅ ጭምቆ ይባላል፡፡ ማር ሊጨመርበት ይችላል፡፡

ማጠቃለያ

ዳጉሳን የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከብዙ ዘመናት ጀምሮ በመዝራት እስከዛሬ አቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ዳጉሳ በምርምር እና በስነምግብ ረገድ ልዩ ትኩረት አልተቸረውም፡፡ ከቶም በአደባባይ የሚታወቀው “የዳጉሳ ጠላ በጎን የሚነዳ . . . ” በሚባለው ዘፈን ነው፡፡ ዳጉሳ ስነምግቡን የዓለም የሥነምግብ ባለሙያዎች በደማቁ ጽፈውለታል፡፡ ዳጉሳ ለእንስሳት መኖም በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ እንዲሁም መድኃኒት ጭምር፡፡  እንደዚህ ዛሬ ድርቅ እና የአየር ፀባይ በመለዋለጥ አሳር በሚያሳይበት ዘመን ዳጉሳ ተመራጭ መሆን አለበት፡፡ መጠባበቂያ ዘር ቢሆን ሽረት ነው፡፡ አንድ ሌላ ሰብል ቢጠፋ ዳጉሳን መተካት ይቻላል፡፡ ዘሩም በጥንቃቄ ቢዘራ ለአንድ ጥማድ ሁለት ኪሎ ይበቃል፡፡ ለሄክታር አሥር ኪሎ በቂ ነው፡፡

በእኛ አገር ገና ብዙ ያልተጠና፣ የጎላ እውቅና ያልተቸረው እና በአርሶ አደሩም ሆነ በሸማቹ ህዝብ ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን ቀረብ ብለው ያጠኑት ጥቂት ተመራማሪዎችና አምራቾቹ ስለምግብና የመድሀኒትነት ፋይዳው ብዙ የሚሉለት ዳጉሳ፤ እንዲሁ ጠላ  እና አረቄ የመሳሰሉ ባህላዊ መጠጦቻችን አዳማቂ ሆኖ የሚቆየው እስከመቼ ይሆን?

አንባቢ ሆይ በጽሁፌ መጀመሪያ ላይ ካነሳሁት ያልተዜመለት የእህል አባት- ዳጉሳ   ከሚለው ጥያቄ መሰል ርዕስ በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እራሳችሁን ጠይቁ ወይም ከሌሎች ጋር ተወያዩበት፣

  • ዳጉሳን በብዛት ያልዘራነው ወይም ያልተመገብነው ለምንድነው?
  • ወደፊት ዳጉሳን ለምግብነት ለመጠቀም ምን ማድረግ አለብን?
  • እርሻውን ለማስፋት ከማን ምን ይጠበቃል?
  • እኛ አገር በዳጉሳ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ምን ይነግሩናል?
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com