ቅምሻ – ከወዲያ ማዶ # ካሜራ አምራቹ ኮዳክ ወረርሽኙን ለመዋጋት መድሃኒት ወደ ማምረት ገባ

Views: 184

ካሜራ በማምረት የሚታወቀው ግዙፉ የአሜሪካ ድርጅት ኮዳክ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት መድሃኒት ወደ ማምረት ሥራ መግባቱ ተገለፀ።

ድርጅቱ ለዚህ ሥራውም ከአሜሪካ መንግሥት የ765 ሚሊየን ገንዘብ ብድር ያገኘ ሲሆን የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ለመድሃኒቶች የሚሆኑ ግብዓቶችን ያመርታልም ተብሏል።

ብድሩ መሰጠቱ ይፋ በተደረገበት ጊዜም የአሜሪካ መንግሥት ለሕክምና አቅርቦት በሌሎች አገራት ላይ ጥገኛ መሆኑን መቀነስ እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ማክሰኞ ዕለት ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ የኮዳክ አክሲዮኖች ከ60 በመቶ በላይ ጨምረዋል።

የድርጅቱ ኃላፊ ጂም ኮንቲንነዛም “አሜሪካ በዚህ ረገድ ራሷን እንድትችል የመድሃኒት ግብዓቶችን በማምረት የዚህ አካል በመሆኑ ኮዳክ ኩራት ይሰማዋል። ” ብለዋል።

የመድሃኒቶቹን ግብዓቶች በስፋት ለማምረትም ሦስት ወይም አራት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ኃላፊው አክለዋል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ፒተር ናቫሮ በበኩላቸው ” ከዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከተማርን፤ የተማርነው፣ አሜሪካዊያን በጣም አስፈላጊ ለሆኑ መድሃኒቶቻቸው በውጭ መድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ  ጥገኛ መሆናቸውን ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ኮዳክ ትልቅ የአሜሪካ ካምፓኒ መሆኑን በመጥቀስ “በአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ ከሆኑ ስምምነቶች አንዱ ይህ ነው” ብለዋል።

የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት እየተሽቀዳደሙ ሲሆን የተወሰኑትም በሰዎች ላይ እየተሞከሩ ነው።

ኮዳክም ወደ መድሃኒት ማምረት ሥራ የገባ ብቸኛ የፎቶግራፍ ድርጅት አይደለም። ከዚህ ቀደምም የጃፓኑ ፉጂ ፊልም ተስፋ የተጣለበት የኮቪድ-19 ክትባት እየሰራ ይገኛል። ይህ ክትባት በቅርቡ ሰው ላይ ይሞከራል ተብሎም ይጠበቃል።

ኮዳክ ካምፓኒ የተመሰረተው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1888 በጆርጅ ኢስትማን ነበር።

ካምፓኒው መድሃኒት ማምረት የጀመረው ከአራት ዓመታት በፊት ቢሆንም አሁን ግን በአስደናቂ ሁኔታ በኒዮርክና ሜኒሶታ በሚገኙት ተቋማቱ ሥራውን እያስፋፋ ነው።

ቢቢሲ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com