በክዊት (buckwheat)፣ ግሉቲን አልባ ምርጥ የህል ዘር፣ (ክፍል አንድ)

Views: 157

መነሻ

በዓለም ላይ የዛሬ ምርጥ የጤና ምግብ እና የነገ ምርጥ የተስፋ ቁንጮ እህል ከተባሉት አራት እህሎች አንዱ በክዊት ነው፡፡ በክዊት (buckwheat) በሳይንሳዊ አጠራር ፋጎፔረም እስኪዩሌንተም   (Fagopyrum esculentum) ይባላል፡፡  በክዊት ነቅመነሻው መካከለኛ እና ምዕራብ ቻይና መሆኑ ይነገራል፡፡ በቻይና አንድ ሺ አመታት በላይ ሲታረስ ነበር፡፡ ከዚያም በመካከለኛው ዘመን ወደ አውሮፓ ወስደውት ማምረት ተጀመረ፡፡  የዕህሉ ዝርያ ከስንዴ ጋር አንድ አይደለም፡፡ እንዲሁ መጠሪያው በክዊት ይባላል እንጂ፡፡

በ2ዐ14 እ.ኤ.አ  በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ መሠረት በከፍተኛ መጠን የሚያርሱት 1ዐ (አሥር) አገራት፣ ራሽያ፣ ቻይና፣ ዩክሬን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ዩ.ኤስ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ካዛኪስታን፣ ሊቱዋኒያ (Lithuania) እና ጃፓን ናቸው፡፡ ከአፍሪካ ከፍ ያለውን ድርሻ ያላት ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ (ማጣቀሻ 2)

1ኛ/ በክዊት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ

በክዊት በአገራችን በሆለታ እና ባኮ እርሻ ምርምር ተሞክሯል፡፡ ግን በአካባቢው አልተስፋፋም፡፡ ለመረጃም በገበያ ላይ የለም፡፡ ምናልባትም ትኩረት አልተሰጠው ይሆናል፣ የገበያ ትስስር አልተዘረጋ ይሆናል ወይም በሌሎች የተለያዩ ችግሮች የተነሳ አልተስፋፋም፡፡ በሚበቅልበት ደጋ እና እርጥብ ወይና ደጋ አካባቢ ተስማሚ በሆነ አፈር፣ እጅግም ልምላሜ በሌለው መሬት ላይ በ 3 ወር ጊዜ ይደርሳል፡፡ ብቻ ውርጭን አይወድም፡፡ ሸክላ አፈርና ልምላሜ የበዛው የአፈር ዓይነት በስተቀር በብዙ የአፈር ዓይነት ላይ ሊለማ ይችላል፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ የበዛ ንፋስ እና ዝናብ አይፈልግም፡፡

2ኛ/ በክዊት ዋና ጠቀሜታው

በክዊት ዋና ጠቀሜታው ለሰው ልጅ ምግብ፣ የእንስሳት መኖ እና መሬትን ለማዳበር ወይም ጦምአደር (as a cover crop) እንዳይሆን መዝራት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በምሥራቅ የአውሮፓ አገራት ለአቼቶ፣ ለቢራ፣ ለአልኮል መጠጥ እና ለሻይ ይሆናል፡፡

Special qualities  (ማጣቀሻ 3)

  • gluten-free and is suitable for coeliacs;
  • Contains rutin, a compound that prevents blood from clotting.

Importance for small scale farmers

  • cold and drought tolerant with a short growing season (2-4 months) and can be cultivated as a second crop;
  • does well in areas of high elevation (up to 4500 m) or those with a short frost-free period;
  • Useful for attracting pollinators for producing honey.

3ኛ/ በክዊት አበቃቀሉ

በክዊት በማበብ ላይ ሳለ

አበቃቀሉ ቀጫጭን ውስጠ ክፍት የሆኑ ቀላ ያሉ ዘንጎች  እና ሰፋ ያሉ ልበ ቅርፅ ያላቸው ቅጠሎች አሉት፡፡ ቁመቱ እንደ ዓይነቱ ከግማሽ ሜትር እስከ አንድ ሜትር ተኩል ይሆናል፡፡ ብዙ ቅርንጫፎችም አሉት፡፡ ዘንጎቹ እንደሸንበቆ ክፍት ስለሆኑ አቅም ስለሚያንሳቸው ለመውደቅ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ማበብ ይጀምራሉ፡፡ አበባው ነጭ፣ ወይም ነጣ ያሉ ወይንጠጅ እና ከላይ በምስሉ እንደሚታዩት ችምችም ያሉ ናቸው፡፡

በክዊት ደርሶ እንደታጨደ ከነአገዳው

ከላይ በምስሉ ላይ ያለው በ2ዐዐ9 ዓ.ም አርሲ በቆጂ ጨፋ ውስጥ ለሙከራ የዘራሁት እና በሶስት ወር ደርሶ የታጨደ በክዊት ከነአገዳው የነበረ ነው፡፡

4ኛ/ በክዊትን ለማረስ ምን መነሻ ነበረኝ

በ2ዐዐ5 ዓ.ም አንድ አሜሪካዊ  ጤፍ እና በክዊትን በማመጣጠን የጤና ምግብ  የሚያመርት  አዲስ አበባ መጥቶ እንደዚህ ይለኛል፡፡ እኔ አሜሪካ ውስጥ የጤና ምግብ አምራች ነኝ፡፡ የማመርተውም ለፓን ኬክ የሚሆን ኦርጋኒክ የሆነ፤ ጤና ምርጥ የዱቄት ዓይነት ሲሆን፤ ጤፍ እና በክዊት ቀይጬ ነው፡፡ አሁን ከዚህ ጤፍ ልገዛ ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጤፍ ወደ ውጪ እንዳይወጣ ከለከለች፡፡ ካገኘሁ ከኬንያ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን  በክዊት ከዚያው ከአሚሪካ ይገኛል፡፡  ጤፍን እስከ ዛሬ ከእስፔን እየገዛሁ ነበር፡፡ ጤፉ ግን ከኢትዮጵያ ባገኝ ይሻለኝ ነበር፡፡

ይቺን ቁምነገር ወሬ ባገኘሁበት ፍጥነት በክዊት ከወዴት ይገኛል ብዬ ማስፈለግ ጀመርኩኝ፡፡ በጊዜው ማግኘት አልቻልኩም ነበር፡፡ በ 2ዐዐ7 ዓ.ም ክረምት ወራት መግቢያ ላይ እንደምንም ብላ የወንድሜ ልጅ አንድ ኪሎ በክዊት ሰጠችኝ፡፡ ሁለት እግዜር የመረቃቸው ከጭላሎ ግርጌ ከአሰላ በስተምሥራቅ ከፍ ባለው ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች ትንሽ ዘር ሰጥቻቸው ዘሩት፡፡ የእድገቱንም ሂደት በየጊዜው ነገሩኝ፡፡ አንዴም ሁለት ወር ሆኖት ማፍራት የጀመረውን ነቅለው ላኩልኝ፡፡ ፍሬው መልካም ይዞ ነበር፡፡  ሶስት ወር ሲሆነው እንዴት እንደሚሰበስቡት በስልክ ተነጋገርን፡፡ አዘመሩት፡፡ በመቀጠል ጥር 2ዐዐ8 ዓ.ም በመስኖ ውሃ ደግመው ዘርተውት ማበቡን ነገሩኝ፡፡  በወቅቱ በክዊት በደረሰበት ይላመዳል ስል ትልቅ ተስፋ አረኩኝ፡፡

በዚህ ሂደት ነበር በ2ዐዐ8/2ዐዐ9 ዓ.ም የአዝመራ ዘመን ለሙከራ ለመዝራት የደረስኩት፡፡  የተሰበሰበውን ጥቂቱን እንዲዘሩት ለሰው ሰጠን፣ ጥቂቱንም ለጤፍ አጃቢ አድርገን፣ ለወፍጮ ቤት አስተዋውቀነው፡፡ እንጀራም ጋገርነው፡፡ ነገር ግን ተመላልሶ በበቆጂ ምድር እንዲዘራ አካባቢውም እንዲለምድ፣ ብዬ ባደረኩት ጥረት ያልተመቸ ክስተት ገጠመኝ፡፡

5ኛ/ በክዊት ዘሩ

ዘሮቹ ከሥር ሰፋ ብለው ከላይ ጠበብ ያሉ እንደ ሶስት ማዕዘን ቅርፅ አላቸው፡፡ የዘሮቹ ቀለም ቡናማ፣ ነጣ ያለ ቡናማ ወይም ጠቆር ያለ ሲሆን፣ መጠናቸው እንደ ዓይነታቸው ይለያያሉ፡፡  ምስሉ ላይ የምትመለከቱ ነጣ ያለ ቡናማ መልክ ያለው ነው፡፡ ምስሉ የተገኘበት መረጃ መረብ ከታች ተጠቅሷል፡፡

Image two Buckwheat seeds

በክዊት በእኛ አገር በተገቢው ያልተስፋፋበት ከዋነኛ ምክንያት ውስጥ አንዱ፤ እህሉ እንደ ቅርፊት መሳይ ጠንካራ ሽፋን ስላለው ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ ሽፋን የሚፈለፍል የተለየ ማሽን ያስፈልጋል፡፡ የተለመደው ወፍጮ በደንብ አይፈለፍለውም፡፡

6ኛ/ የበክዊት ሽፋን ባለዋጋ ነው፡፡

በእኛ አገር በክዊት በጠንካራ ሽፋኑ የተነሳ እና መፈልፈያ ባለመኖሩ ተወዳጅ አለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጠንካራ ሽፋኑ ለነቀዝ እና ለአንዳንድ ተባዮች እንዳይጋለጥ ይረዳዋል፡፡ እናም ሳይፈለፈለ በደረቅ ቦታ ከተቀመጠ ከተመረተበት ጊዜ አንስቶ ከሶስት አመታት በላይ መቆየት ይችላል፡፡ ጠንካራ ሽፋኑ የውስጡን እህል በመጠበቅ ለበክዊት ያለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው፡፡ 

7ኛ/ በክዊት የምግብ አሠራር

እስከ አሁን የታወቀው ምግብ አሠራር በአውሮፓ ለገንፎ (እነሱ ፖሬጅ የሚሉት)፤ ለሾርባ፣ ከሰላጣ ዓይነት ጋር ወይም ለቁርስ የሚሆን እህል ነው፡፡ የካናዳ ምግብ አቀናባሪዎች በክዊትን ለፓንኬክ ቅይጥ፣ ለዳቦ እና ለሌላም ይጠቀሙታል፡፡ በካናዳ የሚመረተውን ዋነኛ ገዢ ጃፓን ስትሆን፤ የምግብ አቀናባሪዎቿ በክዊትን አስፈጭተው ከስንዴ ዱቄት ጋር ቀይጠው ሶባ ኖድልስ ወይም በክዊትኖድልስ (“Soba” or buckwheat noodles.) ያመርታሉ፡፡ የጃፓን ተጠቃሚዎች ጥራት ያለውን ሶባ ኖድልስ ለመምረጥ ልዩ ናቸው ይባላል፡፡ እናም ይህ ለእነሱ አዲስ ሰብል የሆነው በክዊት ብቻ ነው የሚፈልጉትን ቀለም እና ቃና ያለው፡፡ ጃፓኖች በክዊትን እራሳቸውም በብዛት አምራች ናቸው፡፡

በምግብ አሠራር በማንኛውም መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፡፡ በዓለም ላይ ስንዴን ተክቶ የጤና ምግብ ለማዘጋጀት ይጠቅማል፡፡ አሁን እጅግ ለመንገር የተፈለገው ግን ከጤፍ ጋር ተቀይጦ የሚዘጋጀው ዱቄት ምርጥ የምዕራባውያን ፓንኬክ፣ ዋፍል ወይም ፒሳ ለመሥሪያ መሆኑን ነው፡፡

ስለምግብ አሠራሩ ትንሽ ጭማሪ (ማጣቀሻ 3)

How to eat it

Stir-fried buckwheat noodles with vegetables

Ingredients: 2 cups cooked buckwheat noodles (prepared as per instructions on packet); 1-2 tablespoons of cooking oil; 1 medium onion; 1-2 cloves garlic; 1/2 head cabbage chopped ; 1-2 carrots chopped; 1/2 cup of other mixed vegetables, such as chopped broccoli or whole fresh peas in the pod; 2 tablespoons soy sauce

Preparation: Finely chop the onion and garlic and sauté over medium heat in oil. Add the vegetables and soy sauce and cook over medium heat for a further 7-8 minutes or until vegetables are soft. Finally, add two cups cooked buckwheat noodles and simmer for 5-10 minutes. Garnish with chopped almonds or toasted sesame seeds. Serves  4.

በሰላጣ ዓይነትም ከተለያየ አትክልት ጋር ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ከታች ምስሉን ተመልከቱ፡፡

Image three Buckwheat salads -2

8ኛ/ በዓለም ገበያ ላይ

ከዱቄትም ሌላ በተለያየ ዓይነት ለገበያ ይቀርባል፡፡ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ውስጥ ለምሳሌ በዚህ ዓይነት በየሱፐርማርኬት ማግኘት ይቻላል፡፡

Image  four Buckwheat roast seeds

9ኛ/ አስፍታችሁ እረሱ ወይም አሳርሱ

የበክዊት እርሻ እጅግ ቀላል መሆኑን ላስረዳ እወዳለሁ፡፡ እመኑኝ ቀላል ነው፡፡ ልምላሜ የሌለው አፈር ይመርጣል፣ ኬሚካል ማዳበሪያ አይፈልግም፡፡ አዝመራውን መሰብሰብም ቀላል ነው፡፡ በአገሪቱ የትኛውም ደጋ ምድር ይለማል፡፡ በተለይ የአርሲ ባሌ ደጋ ምድር፣  የጎንደር እና ጎጃም ደጋ ምድር እና ሌሎችም ደጋ አካባቢዎች ይሆናል፡፡ ጥቂት ጥረት ይበቃዋል፡፡ ትንሽ  ስለ እህሉ ማንበብ፣ ጥቂት ገበሬዎችን እና የእርሻ ባለሙያዎችን ማነጋገር ነው፡፡ ሆለታ እና ባኮ እርሻ ምርምር ትብብር መጠየቅ ደግሞ እጅግ መልካም ጉዳይ ነው፡፡

 1ዐኛ/ ቅድመ ሁኔታ

 አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቢኖር መፈልፈያውን ማምጣት ወይም ማስመጣት ብቻ ነው፡፡ መፈልፈያውን ከህንድም ቢሆን ከቻይና ማስመጣት ወሳኝ ነው፡፡

ማጠቃለያ

የዛሬው ማጠቃለያ በክዊት ትኩረት ያሻዋል ብዬ ለመወትወት ነው፡፡ ጤፍ ባለ ዋጋ ከሆነበት ምክንያት አንዱ ከግሉቲን ነፃ መሆኑ ነው፡፡ በክዊትም ከግሉቲን ነፃ ነው፡፡ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ገበያ ተፈላጊ ነው፡፡ ልክ እንደ ጤፍ ትኩረት ልንሰጣቸው ከሚገቡን ሰብሎች አንዱ ስለሆነ ነው፡፡ የበክዊትን ጉዳይ ጤፍ የኛ በረካ በሚለው መጽሐፌም ላይ ጽፌው ነበር፡፡ አሁን በዚህ አምድ ላይ ደግሜ ያነሳሁበት ምክንያት መቸም ቢሆን በመላ አገሪቱ በማንኛውም መንገድ፤ ትኩረት እንዲሰጠው ለመወትወት ነው፡፡ አንባቢ ሆይ ተጨማሪ መረጃ ካላችሁ አክሉበት፡፡

 ክፍል ሁለት ወደፊት ይቀርባል፡፡   

ማጣቀሻ፣

  1. በቀለች ቶላ (መጋቢት 2ዐዐ8 ዓ.ም) ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር፣ አርትስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ
  2. https://www.mapsofworld.com/world-top-ten/buckwheat-producing-countries.html
  3. http://www.fao.org/traditional-crops/buckwheat/en/
  4. for image No  1, 2, 3, 4, credit to

https://www.google.com/search?q=buckwheat+foods&client=firefox-b-ab&tbm=isch&source=iu&ictx=1&fir=kbd

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com